Jump to content

ጋን ዪንግ

ከውክፔዲያ

ጋን ዪንግ (甘英) በ89 ዓ.ም. በቻይና አበጋዝ ባን ቻው ወደ ሮማ የተላከ የቻይና ተልእኮ ተወካይ ነበር። ወደ ጳርቴ ምዕራብ ጠረፍ ከገሰገሱት ከባን ቻው ሳባ ሺህ ጭፍሮች አንዱ ነበር።

ጋን ዪንግ ምናልባት እስከ ሮማ ከተማ ድረስ መቸም ባይደርስም፣ በታሪካዊው መዝገብ እንደተመለከተው ከቻይናውያን ሁሉ በጥንት ወደ ምዕራብ የተጓዘው እሱ ሲሆኑ የተቻለውን መረጃ ስብስቦ ተጽፎ ነበር።

ሆው ሀንሹ በተባለው በቻይና ኋለኛው ሃን ስርወ መንግሥት (17-212 ዓ.ም.) ዜና መዋዕል ታሪክ ዘንድ፦

«በዘጠነኛው አመት (89 ዓ.ም.) ባን ቻው ምክትላቸውን ጋን ዪንግ ልከው እስከ ምዕራባዊው ባሕር ድረስ አማተሮ ተመለሰ። የቀደሙት ትውልዶች እነኚህን አቅራቢያዎች ከቶ ደርሰው አያውቁም ነበር። ሻንጂንግ የተባለው መጽሐፍ ስለነሱ ምንም ወሬ የለበትም። ስለነርሱ ልማዶች ምርመር እንዳዘጋጀ ብርቅና ትንግርት ዕቃዎቻቸውንም እንደ ተመራመረ አይጠራጠርም።»
«በዘጠነኛው የዮንግዩዋን አመት (89 ዓ.ም.) በንጉስ ሄ ዘመን፣ ጠባቂ አበጋዝ ባን ቻው ጋን ዪንግን ወደ 'ዳ ጪን' (የሮማ መንግሥት) ልከውት ነበር። እስከ 'ትያውጅር' (ካራቄኔ) እና ሶስያና ድረስ ከታላቅ ባሕር አጠገብ ደረሰ። እሱንም መሻገር ፈልገው ነበር፣ ነገር ግን የአንሺ (ጳርቴ) ምዕራብ ጠረፍ መርከበኞች እንዲህ አሉት፦
'ውቅያኖስ እጅግ ታላቅ ናትና ደርሶ መልስ ያደረጉ ንፋሶቹ ተስማሚ ከሆኑላቸው በሦስት ወሮች ውስጥ ሊጓዙት ይችላሉ። ዳሩ ግን የሚያቆዩህ ንፋሶች ቢያጋጥሙህ ሁለት አመታት ሊፈጅ ችሏል። ስለዚህ በባሕር ላይ የጓዙ ሰዎች ሁሉ የሶስት አመት ስንቅ ይወስዳሉ። ሰፊው ውቅያኖስ ሰዎች ስለ አገራቸው እንዲያሰቡ ይግፋፋቸዋል አገራቸውንም በጣም ይናፍቃሉ አንዳንዶችም ይሞታሉ።'
ጋን ዪንግ ይህንን ሰምቶ አሳቡን ለቀቀው።»

ሆው ሃንሹ ውስጥ በሌላ ክፍል ደግሞ እንዲህ ይላል፦

«የሮማ ግዛት ለብዙ ሺህ [1 ማለት ግማሽ ኪሎሜትር ያሕል] ይዘረጋል። ከአራት መቶ በላይ ባለ-ቅጥር መንደሮች ይገኙበታል። ብዙ አሥሮች ትንንሽ ጥገኛ መንግሥታት አሉት። የመንደሮችም ቅጥሮች የተሰሩ ከድንጋይ ነው። የፖስታ ጣቢያዎች በየስፍራው አቋቁመው ሁላቸውም የተመረጉና በነጭ ቀለም የተቀቡ ናቸው። ጥድና ዝግባ አለ፣ ደግሞም ዛፎችና አትክልት በየአይነቱ።»

ጋን ዪንግ ደግሞ ስለ ሮማ ንጉስ ስለ ኔርቫ መንግስት ስለ ሮማውያንም መልክና ስለ ንግድ ዕቃዎቻቸው እንዲህ ሲል መግለጫ ሰጥቷል፦

«ንጉሶቻቸው ዘላቂ አይደሉም። እነሱ ከሁሉ የገባውን ዕጩ መርጠው ይሾሙታል። በግዛቲቱ ላይ ድንገተኛ መቅሰፍት ለምሳሌ ያልተለመደ ንፋስ ወይም ዝናብ ብዙ ጊዜ ቢደርስባት፣ ያለምንም ስነሥርዐት ተሽረው ይተካሉ። የተሻሩትም ዝም ብለው መሻራቸውን ተቀብለው አይቆጡበትም።»
«የዚህ ሀገር ሕዝብ ሁሉ ረጅምና ቅን ናቸው። 'የማዕከል መንግስት' [ቻይና] ሕዝቦች ይመስላሉና ስለዚህ ይህ አገር 'ዳ ጪን' [ማለት ታላቁ ቻይና] ተብሏል። ይህች መሬት የምታስገኝ በርካታ ወርቅና ብር፣ ብርቅ ዕንቁዎችም ያብረቀረቀ ጌኛ፣ 'የብሩህ ጨረቃ ሉል'፣ የ'ሃይጂ' አውራሪስዛጎል፣ ቢጫ ሙጫ፣ የተቀለመ ብርጭቆ፣ ነጭ ኬልቄዶን፣ ቀይ ቀለም ያለው ባዜቃ ድንጋይ፣ አረንጓዴ ዕንቁዎች፣ የወርቅ ፈተል ያለበት ጥልፍ፣ የተሸመነ ወርቅ ፈተል መረብ፣ በወርቅ የተቀባ ረቂቅ ግምጃ በየቀለሙ፣ የአዝቤስጦስም ጨርቅ ናቸው።»
«ደግሞ አንዳንድ ሰዎች፦ ከ'ባሕር በጎች' ሱፍ ተሰራ ነው (የባሕር ሐር) የሚሉት በውኑ ግን ከተፈጥሮ ሐር ትል ጎጆ የተሠራ ረቂቅ ጨርቅ አላቸው። መዓዛዎችን በየአይነቱ ይቀላቁበታልና ጭማቂውን በመፍላት ውሑድ ሽቶ ይፈጥራሉ። ከተለያዩት ውጭ አገሮች የሚመጡ ብርቅና ውድ ነገሮች ሁሉ አሏቸው። የወርቅና የብር መሐለቅ ገንዘብ የሰራሉ። አሥር የብር መሐለቆች ዋጋ እንደ አንድ የወርቅ መሐለቅ ነው። ከ'አንሺ' (ጳርቴ) እና ከ'ትየንጁ' (ስሜን-ምዕራብ ሕንድ) ጋር በመርካብ ይነግዳሉ። የሚተርፉበት ለአንድ እጅ አሥር እጥፍ ነው። የዚሁ አገር ንጉስ ምንጊዜም ወደ ሃን [ቻይናዎች] ተወካዮችን ለመላክ ወድደው 'አንሺ' ግን የተቀለሙት የቻይና ግምጃዎች ንግድ ለመቆጣጠር ፈልገው ሮማውያን ወደ ቻይና እንዳይገቡ መንገዱን አገዱባቸው።»