በወረርሽኙ ምክንያት በ150 ሃገራት የሚገኙ 370 ሚሊዬን ገደማ ተማሪዎች ከምገባ መርሃ ግብር ውጭ ሆነዋል ተባለ
ዩኔስኮ የትምህርት ቤቶቹ መዘጋት በ199 ሃገራት በሚገኙ 1.6 ቢሊዬን ተማሪዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ገምቶ ነበረ
ለተማሪዎቹ ይቀርብ የነበረ ከ39 ቢሊዬን በላይ ምግብ ሳይቀርብ ቀርቷልም ተብሏል
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ በመላው ዓለም በመቶ ሚሊዬን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከምገባ መርሃ ግብሮች ውጭ መሆናቸው ተነገረ፡፡
በመርሃ ግብሩ በታቀፉ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ይቀርብ የነበረ 39 ቢሊዬን ምግብ ሳይቀርብ መቅረቱንም የዓለም የምግብ እና የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅቶች አስታውቀዋል፡፡
መርሃ ግብሩ ተማሪዎች ጤናቸው ተጠብቆ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ የሚያስችል ነበረ፡፡
ሆኖም በወረርሽኙ ምክንያት በመቶ ሚሊኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከመርሃ ግብሩ ውጭ ሆነዋል፡፡
ዩኔስኮ የትምህርት ቤቶቹ መዘጋት በ199 ሃገራት በሚገኙ 1 ነጥብ 6 ቢሊዬን ተማሪዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ገምቶ ነበረ፡፡
በ150 ሃገራት የሚገኙ 370 ሚሊዬን ገደማ ህጻናት ከምገባ መርሃ ግብሩ ሊርቁ ይችላሉም ብሏል፡፡
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመትም የተስተዋለው ይኼው ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ይቀርቡ የነበሩ 39 ቢሊዬን ምግቦች ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
ህጻናቱ በትምህርት ቤቶቻቸው በመደበኛነት ሲያገኟቸው ከነበሩ 10 ምግቦች 4ቱን ወይም 40 በመቶ ያህሉን ሳያጡ እንዳልቀረም ተገምቷል፡፡
ይህ ሁኔታ በአንዳንድ ሃገራት ከፋ ያለ ነው፡፡ በመደበኛነት ሲያገኟቸው ከነበሩ 10 ምግቦች ዘጠኙን የሚያጡም አሉ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም እንደተገኘው መረጃ፡፡
የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብርን ተግባራዊ ያደረጉ በርካታ ሃገራት አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ህንድ፣ብራዚል፣ቻይና፣ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፉ ናቸው፡፡
የምገባ መርሃ ግብሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኝ ቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ያመጣል ለትምህርት ያበረታልም፡፡
ሆኖም ወረርሽኙ 24 ሚሊዬን ገደማ ህጻናትን ከትምህርት ውጭ እንዳያደርግ ዩኒሴፍ እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሰግተዋል፡፡
ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት መርሃግብሩን ለመተግበር ሞክራለች፡፡ ከ3 መቶ ሺ የሚልቁ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተጀመረው መርሃግብር በወረርሽኙ ቢፈተንም አሁንም ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ ከአስተዳሩ የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡