ኔታንያሁ በሳምንታዊ የካቢኔ ስብሰባ ላይ ሀውቲዎች እስራኤል "ከባድ ዋጋ" እንደምታስከፍላቸው ማወቅ ነበረባቸው ሲሉ ዝተዋል
ሀውቲዎች ያስወነጨፉት ሚሳይል ለመጀመሪያ ጊዜ ማዕከላዊ እስራኤል ደረሰ።
የሀውቲ ታጣቂዎች እሁድ እለት ያስወነጨፉት ሚሳይል ለመጀመሪያ ጊዜ ማዕከላዊ እስራኤል መድረሱን ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል ሰሜናዊ የመንን በተቆጣጠረው እና በኢራን በሚደገፈው ቡድን ከባድ ጉዳት ታደርሳለች ሲሉ ዝተዋል።
የሀውቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳርኤ እንደገለጸው ቡድኑ 2040 ኪሎሜትር በሚምዘገዘግ አዲስ ባለስቲክ ሚሳይል በ11 1/2 ደቂቃዎች ውስጥ ጥቃት ሰንዝሯል።
የእስራኤል ወታደራዊ ባለስልጣን ሚሳይሉ ተመትቶ መበታቱን ገልጸዋል።
ሚሳይሉ ተመትቶ ከመክሸፉ ከደቂቃዎች በፊት በቴልአቪቭ ከተማ እና በመላው ማዕከላዊ እስራኤል የማስጠንቀቂያ ደዎሎች ተሰምተው ነበር፤ ነዋሪዎችም በጥድፊያ ወደ መጠለያ ቦታ ገብተዋል።
የሚሳይሉ ስብርባሪዎች በባዶ መሬት እና በባቡር ጣቢያዎች አቅራቢያ አርፈዋል ተብሏል። በጥቃቱ በቀጥታ የተጎዳ ባይኖርም፣ ዘጠኝ ሰዎች መሸሸጊያ ለማግኘት በሚሯሯጡበት ወቅት ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ኔታንያሁ በሳምንታዊ የካቢኔ ስብሰባ ላይ ሀውቲዎች እስራኤል "ከባድ ዋጋ" እንደምታስከፍላቸው ማወቅ ነበረባቸው ሲሉ ተናግረዋል። "ይህን ለማስታወስ የሚፈልግ ቢኖር የሆዴይዳን ወደብ መጎብኘት ይችላል" በማለት ነበር ኔታንያሁ እስራኤል ባለፈው ሀምሌ ወር የፈጸመችውን ጥቃት የጠቀሱት።
የሀውቲ ታጣቂዎች የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከእስራኤል ጋር ለሚዋጋው የፍልስጤሙ ታጣቂ ሀማስ አጋርነት ለማሳየት በእስራኤል ላይ የድሮን እና የሚሳይል ጥቃት እየፈጸሙ ይገኛሉ።
ባለፈው ወር ቴልአቪቭን ለመጀመሪያ ጊዜ ያጠቃችው ድሮን አንድ ሰው መግደሏ እና ሌሎች አራት ሰዎችን ማቁሰሏ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ እስራኤል በሆዴይዳ ወደብ ላይ በፈመችው የአጸፋ ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸው እና 80 የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸው ይታወሳል።
ቀደም ሲል የሀውቲ ሚሳይሎች የእስራኤልን የአየር ክልል ጥሰው መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል።
የሀውቲ የሚዲያ ቢሮ ምክትል ነስረዲን አመር እሁድ እለት በኤክስ ገጹ ሚሳይሉ እስራኤል መድረስ የቻለው "20 ሚሳይሎች ለማክሸፍ ያደረጉት ሙከራ ባለመሳካቱ ነው"፤ ይህን ጥቃት "የመጀመሪያ" ነው ብሎታል።